“ድምጽ ነኝ!”

Written on 10/16/2016
Mamusha Fenta


“አንተ ማን ነህ?” ቢሉት ማዕረጉን ፍለጋ

 ሰባኪዉ ዝም ጭጭ መልስ የለም እርሱ ጋ

“በል ባክህ ንገረን

ደግሞ እንቸኩላለን

ለሚጠባበቁን ወሬ እናደርሳለን፤

እንዲህ የሆነ እንደሁ ዝናህም ይወጣል

አገር ጉድ እያለ በክብር ያጅብሃል።”

ጠብ የሚል ሲጠፋ የሚደረድረዉ

የማዕረግ አይነት የሚከናነበዉ

እንደነበር ሲቆም በአንክሮ እያያቸዉ

አማራጭን ሰጡት እንዲመርጥላቸዉ።

“ክርስቶስ ነህ ኤልያስ ወይስ ነቢዩ ነህ? 

ምንስ ነዉ ማዕረግህ ማን ብለን እንጥራህ?

እባክህ ንገረን  ክብር  ደረጃህን

ስምና መለያ የሚመጥንህን”

ያን ጊዜ ከበደዉ መታገስ አቃተዉ

ማድመጥም አልቻለ እንኳን ሊደርበዉ

የሚጯጯሁትን ቀና ብሎ አየና

“ድምጽ ነኝ”! አላቸዉ እጅጉን ጮኸና

ያመጡትን ኮከብ የሚለጥፉትን

አራግፎ ከላዩ ሰዉ ሠራሽ ማዕረግን 

እንዲህ ሲል ቀጠለ ሰባኪው ጩኸቱን፡-

“ድምጽ ነኝ፣ ድምጽ ነኝ ያዉም የበረሀ

መንገድ የሚያቀና እንዲያልፍበት ዉሀ

እንደልቡ እንዲሔድ ሕይወት ሰጭዉ ጅረት 

ጥርጊያዉን አቅኝ ነኝ በሚሰጠኝ ምህረት 

በሉ አትነዝንዙኝ ማንነቴ ይህ ነው

ሌላ ምንም የለኝ ስለራሴ እምለዉ

ኋላዬ ያለዉ ግን ባለማዕረግ ነዉ

ከሰማይ የመጣዉ ክርስቶስ ጌታዬ 

ከሁሉ በላይ ነዉ።”

 

 (ዮሐ 1፧19-28)